ከኋላ ቀር እና ፍትሃዊነት ከጎደለው የንግድ አሰራር መላቀቅና የምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ።
የአብክመ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸሙ በመገምገም በ2018 በጀት ዓመት ዕቅዱ ላይ ከዞንና ከተማ አስተዳዳር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል። የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ/ር) ተቋማቸው በ2017 በጀት ዓመት የንግድ ሥርዓቱን በማሳለጥ ሕዝቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ መሥራቱን ገልጸው በ2018 በጀት ዓመት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት ይገባል ብለዋል። በፌዴራል ደረጃ በተደረገ የ2017 አፈጻጸም ውድድርም ተቋማቸው በሁለት ዘርፎች በአገር አቀፍ ደረጃ የሁለተኛ ደረጃ ተሸላሚ መሆኑን አውስተዋል። የጥራጥሬ እና ቅባት እህል ኤክስፖርት ላይም የተሸለሙ ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ለውጤቱ የቢሮው የተዋረድ ተቋማት ድጋፍ እና ጥረት ከፍ ያለ መሆኑን በማንሳት አመስግነዋል። ሕገ-ወጥ ደላላን፣ አላስፈላጊ ኬላን እና ሕገ-ወጥ ንግድን መከላከል በ2018 በጀት ዓመት በትኩረት የሚፈጸሙ ተግባራት መሆናቸውን ቢሮ ኃላፊው አሳውቀዋል። ከክልሉን ከኋላ ቀር እና ፍትሀዊነት ከጎደለው የንግድ ሥርዓት የማላቀቅና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን የማሳደግ ስራ በዚህ ተቋምና አጋሮቹ ላይ የተጣለ ትልቅ አደራ መሆኑን አውስተው በየደረጃው ያለ አካል ከነበረው በላቀ የኃላፊነት ሊሰራ እንደሚገባው አሳስበዋል። ጅምሮችን እና ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም የበለጠ መሥራት እና የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን ስኬታማ መሆን ይጠበቃል ነው ያሉት። በዚህም ሕዝቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ዶክተር ኢብራሂም አስረድተዋል። በውይይቱ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላትም ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በትጋት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል ፡፡





