የአብክመ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የውጭ ንግድና ተኪ ምርትን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ ነው ።

የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትንና የወጪ ንግድን ለማሳደግ ሕጋዊ የገበያ ሥርዓትን ማጠናከር ይገባል-የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢብራሂም ሙሀመድ

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የውጭ ንግድና ተኪ ምርትን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጎንደር ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢብራሂም ሙሀመድ፣ የኢንዱስትሪዎችን የግብዓት ፍላጎት ለማሟላት፣ የወጪ ንግድን ለማሳደግና ከገበያው የሚገኘውን የጋራ ጥቅም ለማረጋገጥ ሕጋዊ የግብይት ሥርዓቶችን በተጠናከረ መልኩ መተግበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዶክተር ኢብራሂም በንግግራቸው፣ የክልሉ የግብርና ምርቶች ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ከመሆናቸውም በላይ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ምንጭ በመሆናቸው፣ የምርት ግብይት በውል እርሻ፣ በቀጥታ ግብይትና በኢትዮጵያ ሸቀጥ ገበያ ሥርዓት መሠረት መፈጸም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እነዚህን ሥርዓቶች በአግባቡ መተግበር ላኪዎች በቂና ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኙ፣ ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን ግብዓት በወቅቱ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም መንግሥትና ክልሉ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም በአግባቡ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ እየተስፋፉ የመጡት ኢንዱስትሪዎች በሙሉ የማምረት አቅማቸው እንዲሠሩ የሚያስፈልጋቸውን የግብርና ግብዓት መጠን በመለየት በቂ አቅርቦት ማረጋገጥ የዘንድሮ ዓመት ትኩረት እንደሆነ ጠቁመዋል። በተለይም የደላላና የሕገወጥ ግብይት ተጽዕኖን በመቀነስ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት በተገቢው መንገድ እንዲያገኙ የተቀናጀ ሥራ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በሦስተኛ ደረጃ፣ ሰሊጥ፣ ማሾ፣ ቦሎቄ፣ አተርና ባቄላን ጨምሮ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ወደ ውጭ መላክ እንደሚገባ ገልጸዋል። ለዚህም ላኪዎችን በመለየት፣ ምርቱን ከሚገዙበት ቦታ ጀምሮ እስከ መዳረሻ ወደብ ድረስ ተገቢውን ድጋፍ መስጠት፣ ምርቱን በወቅቱ መሰብሰብ፣ በጥራት ማሸግና በተያዘለት ጊዜ ለገበያ ማድረስ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ እነዚህን የተቀናጁ ሥራዎች በተሻለ ሁኔታ መፈጸም የክልሉን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ፣ ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን በሙሉ አቅም እንዲያመርቱ፣ ተኪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ለማቅረብና የክልሉን አስተዋጽኦ በሀገራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ለማሳደግ ያግዛል።

በመድረኩም የገበያ ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ ለኢንዱስትሪዎች የግብዓት አቅርቦትን ማሻሻልና የወጪ ንግድን ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ታቅዷል።

በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል የህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌትነት አማረ፣ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አትክልት አሳቤ፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻውን አቶ እድሬስ አበዱ የአብክመ ኢንዱስትሬና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top